ትምህርተ ህቡአት

ትምህርተ ኅቡዓት

በእንተ ትምሕርተ ኅቡዓት ቅድመ ዘትትነገር እምጵርስ ፎራ

ኅቡዓትን ስለመማር ኅቡዓትን ስለማስተማር ስጋውን ደሙን ከመቀበል አስቀድሞ የምትነገር ትምህርት ይህች ናት፡፡ ኅቡዓት ያላቸው አምስቱ አእማደ ምስጢርን ናቸው፡፡ ኅቡዕ ማለት ለመልካም ነገር የተደበቀ አብነትን ምስጢር አድርጎ ለተጠሩትና ለተመረጡት የሚገለጥ፣ የሚሰጥና ለአመኑት ብቻ የተፈቀደ: ላላመኑት ግን የተደበቀ፣ የማይገለጥ፣ የማይሰጥ ማለት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ስለዚህ ምስጢርን ለማዎቅ የተፈቀደላቸው የሚማሩት የኪዳን ትምህርት ሲሆን ትምህርተ ኅቡዓት ከሰባቱ ኪዳናት የሚመደብ በመሆኑ ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ አስቀድሞ ስለ አምስቱ አእማደ ምስጢር በትምህርተ ኅቡዓት እንዲሰጥ ተደረገ፡፡

እንደ አባተቶቻችን አስተምህሮ ሰባቱ ኪዳናት የሚባሉት የመጀመሪያው ትምህርተ ኅቡዓት ሲሆን ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔር ወይኑም ተለውጦ ደመ ወልደ እግዚአብሔር የሚሆንበትን የኪዳን ምስጢር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው የመጀመሪያው የኪዳን ምስጢር ነው፡፡ ሁለተኛው ዘጠኙ ኪዳናት ናቸው፡፡ በመንፈቀ ሌሊት በጽባሕና በሠርክ የሚቀርቡ የምስጋና ኪዳናት ናቸው፡፡ እነዚ ኪዳናት የእግዚአብሐየርን ደግነት፣ በጎና ድንቅ ሥራውን ይናገራሉና ካህኑ ለምዕመናን በተመደበላቸው ጊዚያት እየከፋፈለ እንዲጸልይላቸው ይደረጋል፡፡ ትምህርቱ የጌታ ነው፡፡

ሦስተኛው እግዚአብሔር ዘብርሃናት ይባላል፡፡ የዚህ ኪዳን ትምህርት እራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማራቸው የኪዳን ትምህርቶች የተወሰደ ሆኖ ከሰባቱ ኪዳናት በሦስተኛ ደረጃ ይመደባል፡፡ አራተኛው በእንተ ቅድሳት ይባላል፡፡ ይህ ኪዳን ከዲያቆናት እስከ ሊቀ ጳጳሳት ከ ፏደሬ እስከ ንጉሥ ወይም መሪ እንዲሁም ለምዕመናን፣ ለእንስሳት፣ ለአዝርዕትና ለአትክልቱ ሁሉ የሚጸለይ ታላቅ የምልጃ ኪዳን በመሆኑ አራተኛውን ደረጃ ይዟል፡፡ አምስተኛ ‹‹ በሰማይ የሀሉ ›› ሲሆን ዲያቆኑ ካባ ላንቃውን ለብሶ ዘውድ ደፍቶ መስቀሉን ይዞ ከፍ ካለ ቦታ ሆኖ አስቀድሞ ‹‹ እመቦ ዘቦ ነውረ ሕሊና ይትከላዕ ወኢይቅረብ... ››ን በዜማና በንባብ ያቀርባል፡፡ ይህ ኪዳን የእግዚአብሔርን ታላቅነት፣ ፈራጅነትና ፍጹም የምህረትና የቸርነት ባለቤት እንደሆነ የሚያስተምረን ነው ፡፡ ይህን ፈራጅነቱን ለሚጠራጠር ነውር ያለበት፣ ቂምና በቀል የያዘ ቸርነቱን የማይለምን የሚወገዝበት የትምህርት ክፍል በመሆኑ በአምስተኛ ደረጃ ላይ የተመደበ ኪዳን ነው፡፡

በስድስተኛ ደረጃ ቅዳሴ እግዚእን እናገኛለን፡፡ ይህ የኪዳን መጽሐፍ እንደአባቶቻችን አስተምህሮ ደራሲው እራሱ የቸርነት ጌታ የምህረት ባለቤት እኛን በፍጹም ፍቅሩ እስከሞት ድረስ ወድዶን በመልዕልተ መስቀል የገለጸልን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ የቅዱስ ሥጋውንና የክቡር ደሙን አዳኝነትና ፈዋሽነት የምንማርበት ኪዳን ነው፡፡ ሰባተኛ ቅዱስ ስሉስ ነው፡፡ ይህ ጸሎት ኅብስቱ ወደ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔር ወይኑ ወደ ደመ ወልደ እግዚአብሔር ከተለወጠ በኋላ ‹‹ ዘኮነ ንጹሐ ይንሣዕ እምቁርባን ›› በማለት ካህኑ በአዋጅ የፈቀደላቸው ምዕመናንና ምዕመናት ሲቀበሉት የሚጸለይ ኪዳን ነው፡፡ ይህን ኪዳን ሕዝቡ የሚያውቁት ከሆነ እራሳቸው ሥጋውንና ደሙን እየተቀበሉ ይጸልዩታል፡፡ እነርሱ ካላወቁት ካህኑ ሊጸልይላቸው ይገባል፡፡ በማለት ሰባቱን ኪዳናት እንድንማርባቸውና እንድንገሰጽባቸው ሥርዓት ተሰጥቶናል፡፡

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ትምኅርተ ኅቡዓትን ስናነሳ ሁሉንም የኪዳን መጻህፍት በስም ልናነሳቸውና ቀድመን እንድናውቃቸው ወድደን ለግልጽነት አቀረብናቸው እንጂ በዚህ ጽሑፍ በዋናነት ማቅረብ የተፈለገው የመጀመሪያውን የኪዳን ትምህርት ትምህርተ ኅቡዓትን ነው፡፡ ትምህርተ ኅቡዓት ምድቡ ከሰባቱ ኪዳናት ሆኖ በርካታ ምስጢራትን አካትቶ በመያዝ ለአስተምህሮ የተመቸ መጽሐፍ ነው፡፡ የትምህርቱ ጭብጥና ፍሬ ነገር የሚያተኩረውና የሚያጠነጥነው አምስቱን የምስጢር አምዶች መነሻና መሠረት በማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹ በእንተ ትምህርተ ኅቡዓት ቅድመ ዘትትነገር እምጵርስ ፎራ ›› በማለት አምስቱን አእማደ ምስጢር በማስተማር ይጀምራል፡፡

አምስቱ አእማደ ምስጢር እነማናቸው ቢሉ የመጀመሪያው ምስጢረ ሥላሴ ነው፡፡ ይህን የሥላሴን ምስጢረ ትምህርት ሊቃውንት በሥርዓተ ቅዳሴ የትርጉም መጽሐፍ ላይ ‹‹ ኅቡዕ ›› ብለውታል፡፡ ሥላሴ በአካል ሦስት በባሕርይ፣ በሕልውና፣ በአገዛዝ አንድ ናቸው ብለው ፫፻፲፰ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አስተምረዋል፡፡ ሥላሴ አንድ ሲሆኑ ሦስት ሦስት ሲሆኑ አንድ እንደምን ይሆናል ብሎ ልብ ሊመረምረው ቃል ሊናገረው አይችልምና፡፡ ዳግመኛም የሥላሴ ሦስትነትን በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 28 ቁጥር 19 ላይ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባቶቻችን ለሐዋርያት ‹‹ እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ›› በማለት በስም በአካል ሦስትነታቸውን አረጋግጦላቸዋል፡፡ ይንንም ትምህርት አባቶቻችን ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙን ከማቀበል በፊት እንዲሰጥ በትምህርተ ኅቡዓት ትርጓሜ አስተምረውታል፡፡

ሁለተኛውን ምስጢር ምስጢረ ሥጋዌ ኅቡዕ ብለውታል፡፡ በማይመረመርና በረቂቅ ስልጣኑ አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ፤ ረቂቁ ገዘፈ፣ ግዙፉ ረቀቀ ምሉዕ ተወሰነ፤ ውሱኑ መላ ብለው ለሰው ይነግሩታል ያስተምሩታል፡፡ ረቂቅ ሲሆን ግዙፍ ግዙፍ ሲሆን ረቂቅ፤ ምሉዕ ሲሆን ውሱን ውሱን ሲሆን ምሉዕ መሆን እንደምን ይቻላል ብሎ ልብ ሊመረምረው ቃል ሊናገረው አይቻልምና፡፡

ሦስተኛ ምስጢረ ጥምቀትን ኅቡዕ ብለውታል፡፡ ቄሱ ውሀውን በብርት አድርጎ ሥርዓቱን አድርሶ ‹‹ ቡሩክ ›› ብሎ በባረከው ጊዜ ውኃው ተለውጦ በዕለተ ዓርብ ከጎኑ የፈሰሰ ማየ ገቦን ይሆናል ብለው ለሰው ይነግሩታል፡፡ ይህ በብርት የምናየው ውኃ አሁን ተለውጦ እንዲህ መሆን እንዴት ይቻላል ብሎ ልብ ሊመረምረዉ ቃል ሊናገረው አይቻልምና፡፡

አራተኛው ምስጢረ ቁርባንን ኅቡዕ በማለት አስተምረውታል፡፡ ቄሱ ሕብስቱን በጻሕል ወይኑን በጽዋዕ አድርጎ አክብሮ ‹‹ ቡሩክ ›› ባለው ጊዜ ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔር ወይኑ ተለው ተለውጦ ደመ ወልደ እግዚአብሔር ይሆናል ብለው ለሰው ይነግሩታል ያስተምሩታል፡፡ ይህ መሆን እንደምን ይሆናል ይቻላል ብሎ ልብ ሊመረምረዉ ቃል ሊናገረው አይቻልምና፡፡

አምስተኛ ምስጢረ ትንሣኤ ሙታንን ኅቡዕ ብለውታል፡፡ ይህን ምስጢር ሰው ከፈረሰ ከበሰበሰ በኋላ እንደገና አካል ገዝቶ ይነሳል ብለው ለሰው ይነግሩታል ያስተምሩታልም፡፡ ‹‹ በቀዳሚ ንፍሐተ ቀርን ይትጋባዕ ጸበለ ሥጋ ዘተዘርወ ውስተ ኩሉ መካን ኀበ ሀለወ ርእስ፡፡ ወበዳግም ንፍሐተ ቀርን ይሰፈያ አዕፅምት ምስለ ሥጋ ወይከውን በድነ ፍጹመ ዘእንበለ አንሳሐስሐ ወኢተሐውሶ እስከ ጊዜሁ ወበሣልስ ንፍሐተ ቀርንይትነስኡ ሙታን ከመ ቅጽበተ ዓይን ›› በማለት ሲያስተምሩ ሰው ከፈረሰ ከበሰበሰ በኋላ እንደገና አካል ገዝቶ መነሣት እንደምን ይቻላል ብሎ ልብ ሊመረምረዉ ቃል ሊናገረው አይቻልምና፡፡ ስለዚህ ይህን የትንሳኤ ሙታን ትምህረት ኅቡዕ ብለውታል፡፡አንድም ሥጋውን ደሙን ኅቡዕ ብለውታል፡፡ ሲለወጥ አያዩትምና ኅቡዕ ብለውታል፡፡