መዝሙር 0

ዳዊት ማለት ‹‹ኅሩይ›› ማለት ነው። አንድም ‹‹ልበ አምላክ›› ማለት ነው። ሐዋ 13፡22፡፡ ትውልዱ ከነገደ ይሁዳ ነው። አባቱ እሴይ እናቱ ሁብሊ ይባላሉ። ሁብሊ መልከ መልካም ሴት ነበረች። ከጎረቤታቸው ያለ ጎልማሳ መልኳን እያየ በሐጸ ዝሙት ተነደፈ። እሴይ የእሷም ፈቃድ እንደሆነ አውቆ መንገድ እሄዳለሁ ብሎ ስንቁን ይዞ ወጣ። የሄደ መስሎ ከዚያው ውሎ ሲመሽ በልብሱ ተሸፋፍኖ ድምጹን ለውጦ ያንን ሰው መስሎ ገብቶ ከእርሷ ጋር አድሮ ጎህ ሳይቀድ ወጥቶ ሄደ። ዳዊት በዚህ ዕለት ተጸንሷል። “እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ” (መዝ 50፡5) ማለቱ ስለዚህ ነው። ቅዱሱም ተወልዶ ጉልበቱ ከጸና በኋላ የአባቱን በጎች ሲጠብቅ አድጓል።

ንጉሥ ሳኦል ከጌታ ፈቃድ በወጣ ጊዜ እግዚአብሔር ሳሙኤልን ቅብዐ መንግስሥት እንዲቀባው አደረገ። 1ኛ ሳሙ 16፡1-13፡፡ ከዚህ በኋላ በረድኤተ እግዚአብሔር ጎልያድን በአንድ ጠጠር ገደለ። ግዳይ ጥሎ ሲመለስ ሴቶች “ሳኦል ሺህ ገደለ ዳዊት እልፍ ገደለ” እያሉ እየዘፈኑ ተቀበሉት። ቅንዐት አድሮበት ነገር ግን አስቀድሞ ምሎለት ነበርና የመቶ ፍልስጤማውያንን ሸለፈት ተቀብሎ ልጁ ሜልኮልን ዳረለት። አንድ ቀን ሊገድሉት ሲማከሩ ሜልኮል ሰምታ ሽሽ አለችው። ሳዖልም ሶስት ሺህ ሠራዊት ይዞ ተከተለው፡፡ ከሠራዊቱ ተለይቶ ሰውነቱን ለመፈተሽ ዳዊት ካለበት ዋሻ ውስጥ ገባ። ጨለማ ነበርና ሰው መኖሩን አላወቀም። አቢሳ ዳዊትን ጠላትህን አሳልፎ ሰጥቶሀልና ልውደቅበት አለ። ተው ኦሪት ‹‹በእግዚአብሔር መሢሕ ላይ እጅህን አታንሳ›› ትላለችና አይሆንም አለው። እርሱ የልብሱን ዘርፍ በሰይፉ ቀዶ ያዘ። ሲወጣ ተከትሎ ወጥቶ “ንጉሥ ሆይ ዳዊት ቢያገኝህ አይምርህም የሚሉህን ለምን ትሰማለህ እነሆ ዛሬ አሳልፎ ሰጥቶኝ ነበር። ነገር ግን የልብስህን ዘርፍ ከመቅደዴ በቀር ምንም ምን እንዳላደረግሁህ አንተ ታውቃለህ” ብሎ ቅዳጁን አሳየው። ሳኦልም ድምጹን ከፍ አድርጎ በማልቀስ ‹‹ልጄ ዳዊት ሆይ! እኔ ክፉ በመለስሁልህ ፋንታ በጎ መልሰህልኛልና አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ። እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶኝ ሳለ አልገደልኸኝምና ለእኔ መልካም እንዳደረግህልኝ አንተ ዛሬ አሳየኸኝ። ጠላቱን አግኝቶ በመልካም መንገድ ሸኝቶ የሚሰድድ ማን ነው? ስለዚህ ለእኔ ስላደረግኸው ቸርነት እግዚአብሔር ይመልስልህ። አሁንም እነሆ! አንተ በእርግጥ ንጉሥ እንድትሆን የእስራኤልም መንግሥት በእጅህ እንድትጸና እኔ ዐአውቃለሁ›› አለው፡፡ 1ኛ ሳሙ ም 24፡፡ ከዚህም በኋላ ዳዊት በነገሠ ጊዜ ለልጆቹ እንዲራራላቸው ሳኦል ቃል አስገብቶት ወደ ቤተ መንግሥቱ መለሰው። ዳዊት ግን በረሀ በረሀውን ሲዞር ቆይቷል።

በሐቅለ-ፋራን ሳለ ናባል የሚባል ባለጸጋ ድግስ ደግሶ በጎቹን አሸልቶ ሲያበላ ሲያጠጣ ብላቶኖቹ “ምሳ ላክልኝ ብለህ ላክበት” አሉት። “ተው አይሆንም ያለ እንደሆነ እጣላዋለሁ” አለችው። “ይህን ያህል ጊዜ አንዲት ጠቦት እንኳ ሳትነካ ከብቶቹን ጠብቀህለት እምቢ ይላልን ላክበት ግድ የለህም አሉት።” እንኪያስ ሔዳችሁ ንገሩት አለ። ሄደው ቢነግሩት “የማነው ዳዊት” ብሎ አልሰጥም አለ። ዳዊት ይህን ሲሰማ ተቆጥቶ ሊጣላው ተነሳ። ሚስቱ አቤግያ ይህን ሰምታ 5 በግ አሳርዳ አሠርታ፣ 5ቱን አሰናድታ የበለስ የወይን ጥፍጥፍ 500 እንጀራ፣ 12 ጭነት ዱቄት አሲዛ ሄደች። ዳዊት ከመንገድ አገኛትና “ባልሽን ልታድኚው መጣሽን?” ብሎ ያመጣችውን ተቀብሏት ተመለሰ። ናባል ማታ ሰክሮ ነበርና አቤግያ ሳትነግረው አደረች። ሲነጋ ትናንት ዳዊት ሊጣላህ መጥቶ ነበር አለችው። ዳዊት ብሎ ደነገጠ። ልቡን አጥቶ ሰንብቶ በ10ኛው ቀን መልአኩ ቀስፎታል። እመቤታችንና ጌታችን ከአብራኳ አሉና እሷን ግን ኀዘኗን ከጨረሰች በኋላ ዳዊት ሚስት አድርጓታል። 1ኛ ሳሙ ም25፡፡

ከዚህ በኋላ ሳኦል ፍልስጤማውያን በጠላትነት ተነሱበትና ገጠማቸው። ከጠላቶቹ አንዱ ቀስቱን መርዝ ቀብቶ ጎኑን መታውና እንደ እሳት አቃጠለው። ሎሌውን ጠርቶ ገደልነው እንዳይሉ አንተ ጨርሰኝ” አለው። “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ ባሪያህ ካንተ ጋር እሞታለሁ እንጂ እገድልሃለውን?” ብሎ እምቢ አለው። የገዛ ሠይፉን ከምድር ተክሎ ወደቀበት። ሌሎቹም እርሱን አይተው በገዛ ሠይፋቸው እየተወጉ ሞቱ። ዳዊት የርሱንና የልጁ የዮናታንን ሞት ሲሰማ አዘነ። ግጥም እየገጠመ አለቀሰላቸው። ከሳዖል ሞት በኋላ ዳዊት መንግሥቱን አጽንቶ ጽዮንን አቅንቶ ተቀመጠ። ታቦተ ጽዮንንም በዕልልታ በሆታ ወደከተማው አስገባ። የሳኦል ልጅ ሜልኮል ዳዊትን በታቦተ ጽዮን ፊት ሲዘምር አይታ በልቧ ናቀችው። ሲገባ ልትቀበለው ወጥታ “የእስራኤል ንጉሥ በባሪያዎቹ ቆነጃጅት ፊት ዕርቃኑን በመግለጹ ምን ይከብር?” ብላ በአሽሙር ዘለፈችው። በዚህ ቢያዝንባት መካን ሆና ሞታለች። “ሜልኮል እስከምትሞት ድረስ ልጅ አልወለደችም ነበር” እንዲል። 2ኛ ሳሙ ም6፡፡

በዘመኑ የነበረው ነቢይ ቅዱስ ናታን ነው። እርሱም ሊጠይቀው መጥቶ ሳለ አዝኖ አየው። “ምን ሆነህ ታዝናለህ?” አለው። ቅዱስ ዳዊትም “እኔ በጽድ በዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጬ ታቦተ ጽዮን በድንኳን ስትኖር ምነው አላዝን?” አለ። “ጠላት ጠፍቶልሀል፤ መንግሥትህም ጸንቶልሀል አታንጽምን?” አለው። “ያስ ቢሆን ያለፈቃደ እግዚአብሔር ይሆናልን?” አለ። ከዚህም በኋላ ሁለቱም ቀኖና ገቡ። የቤተ መቅደስ ነገር ለናታን ተገልጾለት “አንተ አይደለህም የምትሠራልኝ ከአብራክህ የተከፈለ ልጅህ ይሠራልኛል” ብሎታል። 2ኛ ሳሙ 7፡1-17፡፡ ለቅዱስ ዳዊት ግን የበለጠ የሥጋዌ ነገር ተገልጾለት “እነሆ በኤፍራታ ሰማነው” ብሏል። መዝ 131፡6፡፡

ኢዮአብና አቢሳ ጠላት ለመመለስ ታቦተ ጽዮንን አሲዘው ሠራዊት አስከትለው ወደ አራቦት ዘመቱ። ቅዱስ ዳዊት ግን ከከተማ ቀርቶ ነበር። በሰገነቱ ሲመላለስ ቤርሳቤህን በአፀደ ወይን ውስጥ ስትተጣጠብ አይቷት ፍቅረ ዝሙት አደረበት። “የማን ሚስት ናት?” አለ። “የኦርዮን” አሉት። ኦርዮን ዘምቶ ነበር። “የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ” (ዘጸ 20፡14-17) ያለውን ተላልፎ አስጠርቶ ደረሰባትና ጸነሰች። ጽንስ ያሳስትልኛል ብሎ እቦ ኦርዮንን አስጠርቶ ስለጦሩ ሁኔታ ከጠየቀው በኋላ “ወደቤትህ ሂድ” አለው። ኦርዮን ግን ድንኳን አስተክሎ ከዘበኞቹ ጋር አደረ። “አልመጣም” ብሎ ላከችበት። ዳግመኛም የሚያሰክር መጠጥ አጠጥቶ “ወደቤትህ ግባ” አለው። “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ ታቦተ ጽዮን ተማርካ እስራኤላውያንም ዋዕየ ፀሐዩን ቁረ ሌሊቱን ታግሠው በሜዳ ሲሆኑ እኔ ቤቴ ገብቼ ተድላ ደስታ አደርግ ዘንድ ይገባልን?” ብሎ እምቢ አለ። በማግሥቱ “ኦርዮንን ፊት መሪ አድርጉት ጦሩ ሲበረታ ትታችሁት ሽሹ እሱ በዚያ ይሙት” የሚል ጽፎ አትሞ “ለኢዮአብ ስጠው” ብሎ ሰጠው። የዋህ ነውና የሞቱን ደብዳቤ ይዞ ሄዶ ሰጠው። ኢዮአብ እንደታዘዘው ኦርዮን ከፊት አሳልፈው ጦሩ ሲበረታ ተጠቃቅሰው ወደኋላ ሸሹ። እርሱ መለስ ብሎ “ምን ሆናችሁ?” ቢላቸው ጠላቶቹ ደርሰው ልብ ራሱን ብለው ገድለውታል።

እግዚአብሔርም ለነቢዩ ናታን ተገለጸለት። ናታን ከል ለብሶ ከል ጠምጥሞ ጦር ይዞ ሄደ። ዳዊት “ነቢየ እግዚአብሔር አመጣጥህ በደኅና ነውን?” አለው። “የምነግርህ አለኝ” አለው። “መቶ በጎች ያሉት ሰው ነበር። ከአንዲት በግ ሌላ ምንም ምን የሌለው ጎረቤት ነበረው። መንገድ ሲሄድ አደራ ሰጥቶት ሄደ፡፡ ያ ሰው እንግዳ ቢመጣበት መቶ በጎቹን አስቀምጦ የእርሱን አንዲት በግ አርዶ እንግዳውን ሸኘበት። እርሱንም ለሰው እንዳይነግርብኝ ብሎ ገደለው። በዚህ እግዚአብሔር አዝኗል” አለው። ዳዊትም ይህን ጊዜ “ይህን የሚያደርግ በከተማዬ ካለ ሞት ይገባዋል” አለ። ነቢዩም ወዲያው “ንጉሥ ሆይ! ይህን ሁሉ ያደረግህ አንተ ነህ፣ በራስህ ፈረድህ ባለጸጋ የተባልህ አንተ ደኃ የተባለ ኦርዮን ነው። መቶ በጎች የተባሉ አሥሩ ዕቁባቶችህ ናቸው። አንዲት በግ የተባለች ቤርሳቤህ ናት። እንግዳ የተባለ ፈቃደ ሥጋ ነው። ፈቃደ ሥጋህ ቢነሳብህ 10ሩ ዕቁባቶችህን አስቀምጠህ ከቤርሳቤህ ደረስህ። ኦርዮንንም አስገደልከው። በዚህ እግዚአብሔር አዝኗል” አለው። ይህንንም ሲሰማ ዳዊት ልዋል ልደር ሳይል ዕለቱን ጉድጓድ አስምሶ ማቅ ለብሶ ሱባኤ ይዞ ሌት ተቀን ተንስቅስቆ አለቀሰ፡፡ እግዚአብሔርም ጥንቱን መርጦታልና ጸሎቱን ሰማው። ነቢዩ ናታን ዳግመኛ መጥቶ “በነፍስህ ምሬሀለሁ ብሎሀል። በሥጋህ ግን ኃጢአት ያለፍዳ አይነጻምና ለሦስት ወር ልጅህ መንግሥትህን ይነጥቅሀል፤ ዕቁባቶችን ይቀማሀል” አለው። ዳዊትም “ይህ እንዲሆን በምን ዐውቃለሁ?” አለ። “የሚወለደው ሕፃን ይሞታል፣ እርሷን ግን አግባት ወንድ ልጅ ትወልድልሀለች ስሙን ሰሎሞን ትለዋለህ” አለው። ቀን ከሌት አብዝቶ ያለቅስ ነበርና ከዕንባው ብዛት የተነሣ መሬቱ እርሶ ሠርዶ አብቅሎ ሰውነቱን ተብትቦ ይዞት ነበር። ብላቴኖቹ ቆርጠው አወጡት።

ከዚህም በኋላ ሕፃኑ ተወልዶ ታመመ። “እኔን በነፍሴ እንደማረኝ ሕፃኑንም በሥጋው ይማረው” ብሎ ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ ያለቅስ ጀመር። ሕፃኑ ሞተ፤ ከወደቀበት ተነስቶ ተጣጥቦ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ ማዕድ ቀረበ። ከምሳ መልስ “ታመመ ስንልህ ማዘንህ ሞተ ስንልህ እንዲህ ማድረግህ ስለምንድር ነው?” አሉት። “ውኃ ከፈሰሰ ይታፈሳልን? እንዲሁ ወደርሱ እንሄዳለን እንጂ እርሱ ወደኛ አይመጣም” ብሏቸዋል። ጌታ የተናገረው አይቀርምና ቅዱስ ዳዊት ፍዳን ሊቀበል ሰይጣን የበኵር ልጁ አምኖንን በእኅቱ በትዕማር ፍቅር እንዲያድርበት አደረገ። ኢዮናዳብ የሚባል የአጎቱ ልጅ ሰውነቱ ከስቶ ፊቱ ገርጥቶ ቢያየው “አንተ የንጉሥ ልጅ ሆነህ ምን ያከሳሀል?” አለው። “ፈርቼ እንጂ እኅቴ ትዕማርን ወድጃታለሁ” አለው። “ታመምሁ ብለህ ተኛና አባትህ ሊጠይቅህ መጥቶ ልጄ ብላ ሲልህ በትዕማር እጅ ቢሆን ኖሮ ሁለት ሦስት እንጎቻ በበላሁ ነበር በለው ያዝልሀል” አለው። እርሱም እንደመከረው አደረገ፡፡ ዳዊትም ትዕማርን አስጠርቶ እንድታሰናዳለት አዘዛት። “እኅቴ አንቺን ብዬ እንጂ እህል የሚያቀርብልኝማ መቼ አጣሁ” ብሎ ያዛት። እርሷም “ወንድሜ ይህን አታድርገው እኔን የተናቀች የተጠላች ታደርገኛለህ፣ አንተም ከሰነፎች እንደ አንዱ ትቆጠራለህ” አለቸው። አምኖን ግን በግድ አስነወራት። ወዲያውም ፊት ከወደዳት መውደድ ይልቅ ኋላ የጠላት መጥላት በለጠና ‹‹ውጪልኝ›› አላት። “ከቀደመው የአሁኑ ክፋትህ ይከፋል ተወኝ” አለችው። ብላቴናውን ጠርቶ አስወጥቶ እንዲዘጋባት አደረገ። እርሷም የለበሰችውን ባለህብር ልብስ ቀዳ አመድ ነስንሳ እያለቀሰች ስትሄድ ወንድሟ አቤሴሎም አገኛት። ያስነወራት አምኖን መሆኑን ዐውቆ “ወንድምሽ ነውና አትግለጪበት” ብሎ አጽናንቶ ዳዊት በከተማ ያሠራው ቤት ነበርና ከዚያ አስቀመጣት።

ከሁለት ዓመት በኋላ አቤሴሎም ድግስ ደግሶ ዳዊትን ጠራው። “አስቀድመህ ብትነግረኝ መልካም ነበረ አሁን ግን እኔ ስመጣ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ ወይዛዝርቱ ስለሚከተሉኝ ይበዛብሃል አይሆንም” አለው። “ያም ባይሆን ታላቅ ወንድሜ አምኖን ይገኝልኝ” አለ። እርሱም ‹‹ይሂድልህ›› አለው። ከዚህ በኋላ አምኖን በልቶ ሲጠግብ፤ ጠጥቶ ሲሰክር አቤሴሎም ብላቴኖቹን አዝዞ አስገደለውና እርሱ ወደናቱ ሀገር ጌድሶር ሸሸ። ዳዊት ለልጁ ለአምኖን አለቀሰለት። ከሁለት ዓመት በኋላ አምኖንን እየረሳ አቤሴሎምን እያስታወሰ ሄደ። ቢትወደዱ ኢዮአብ ይህን ዐውቆ አንዲት ቴቁሄያዊት ልኮ አስታረቀው። አቤሴሎም ከአባቱ ጋር ከታረቀ በኋላ በሠረገላ ሆኖ እስራኤልን “ምን ዳኛ አለና ይፈርድላችኋል? እኔማ ይህችን መንግሥት ጥቂት ጊዜ ባገኛት ቀን በፀሐይ ሌሊት በመብራት ፈርጄ ኢየሩሳሌምን አቀናት ነበር” ሲል ሰንብቶ ዳዊትን ለምኖ ሥርዓተ መንግሥት አስወጥቶ ሁለት መቶ መኳንንት ይዞ ‹‹አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ›› እያለ ነጋሪት አስጎሠመ። ዳዊት ይህን ሰምቶ “ኑ ከኢየሩሳሌም እንሽሽ” አለ። ኢዮአብና አቢሳ ግን ‹‹እንዋጋለን›› አሉት። ቅዱስ ዳዊትም ‹‹ጌታ ልጅህ መንግሥትህን ይነጥቅሀል፣ እዋጋለሁ አትበል ብሎኛል አይሆንም›› ብሎ ተራ ልብስ ለብሶ ተራ ጫማ ተጫምቶ ከከተማው ወጥቶ ሦስት ወራት በጫካ ሲያዝን ኖሯል። ከሦስት ወር በኋላ አቤሴሎም ሲዋጋ ሞተ። ዳዊት ወደ ቤተ መንግሥቱ ቢመለስ ዓሥሩ ዕቁባቶቹን ልጁ አርክሷቸው ተገኘ። እርሱም እስከ ፍጻሜ ዘመኑ ሳይደርስባቸው ቀርቷል።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ዳዊት ብዙ ጊዜ ቆይቶ “የባሕርይህን ፍሬ በዙፋንህ ላይ አኖራለሁ›› ያለው ቃል ተፈጽሞለት ልጁ ሰሎሞንን በዙፋኑ አስቀምጦ በነገሠ በ40 ዘመኑ በሰላም ዐርፏል። 1ኛ ነገ 2፡12-14፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ነሐሴ 13 ቀን ተጸነሰ፣ በሚያዝያ 6 ቀን በይሁዳ በቤተልሔም ሀገር ተወልደ። 1ኛ ሳሙ 16፡10-11፡፡ እረኛና ብላቴና የነበረ ቢሆንም የፍልስጤማውያኑን ኃያል ሰው ጎልያድን በ12 ዓመቱ 5 ጠጠርን ከወንዝ ለቅሞ በወንጭፍ ወርውሮ ገድሏል፡፡ 1ኛ ሳሙ 12፡45-51፡፡ ንጉሥ ሳዖል በጌልቦአ ተራራ በራሱ እጅ ከሞተ በኋላ አስቀድሞ በይሁዳ 7 ዓመት በመላው እስራኤል 33 ዓመት ነግሡዋል፡፡ 2ኛ ሳሙ 2፡4፤ 5፡1-5፡፡ ‹‹እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል” (1ኛ ሳሙ 13፡14) ተብሎ በእግዚአብሔር የተመረጠና ነገረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን፣ ዳግም ምጽዓትን፣ ነገረ ማርያምን፣ ክብረ ቅዱሳንን፣ በስፋትና በጥልቀት የተናገረ የብሉይ ኪዳን ‹‹ወንጌላዊ›› የተባለ ቅዱስ ነቢይ ነው። “ብዙ ውሾች ከብበውኛልና የክፋተኞች ጉባኤም ያዘኝ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ። አጥንቶቼ ሁሉ ተቈጠሩ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም። ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ…” እያለ የጌታችንን መከራ መስቀል በትንቢት ተናግሯል፡፡ መዝ 21 (22)፡ 16-18፡፡

“አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።”፣ “ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊት ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ…” እያለ የጌታችንን ዕርገቱንና ዳግመኛ ለፍርድ የሚመጣ መሆኑን በግልጽ ተናግሯል፡፡ መዝ 46(47)፡4-5፣ መዝ 49(50)፡ 1-5፡፡ “የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” እያለ የእመቤታችንን ክብር አይቶ በትንቢት ተናግሯል፡፡ መዝ 44(45)፡9፡፡

ቅዱስ ዳዊት ታላቅና ገናና የከበረ ንጉሥ ከመሆኑ የተነሣ መንግሥቱ የመሢሕ መንግሥት ምሳሌ ሆኗል፤ መሢሑም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት ስም ብዙ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሶ ይገኛል። (ኢሳ 9፡7፣ ኤር 23፡5-6፣ ኤር 33፡14-17፣ ሕዝ 34፡23፣ ሆሴዕ 3፡5) በሐዲስ ኪዳንም ወንጌላዊያኑ ጌታችንን ‹‹የዳዊት ልጅ›› በማለት ነው መጀመሪያ ነገረ ልደቱን ማውሳት የጀመሩት፡፡ ማቴ 1፡1፡፡ ራሱ ጌታችንም ‹‹እኔ የእሴይ ሥርና የዳዊት ዘር ነኝ›› ብሏል፡፡ ራእ 22፡16፡፡

ቅዱስ ዳዊት 7 ሀብታት የተሰጡት ጻድቅ አባት ነው፡፡ እነዚህም የተሰጡት ሀብታት፡- ሀብተ ክህነት፣ ሀብተ መንግሥት፣ ሀብተ መዊዕ (የማሸነፍ ሀብት)፣ ሀብተ ትንቢት፣ ሀብተ ኃይል፣ ሀብተ በገና (ዝማሬ) እና ሀብተ ፈውስ ናቸው። ቅዱስ ዳዊት 24 ሰዓት ሙሉ የእግዚአብሔር ምስጋና እንዳይቋረጥ መዘምራንን መድቦ እንዲያገለግሉ ያደርግ ነበር፡፡ ራሱም 10 አውታር ባለው በገና ሌት ተቀን በፍጹም ተመስጦ ያመሰግን ነበር፡፡ በመዝሙሩም አጋንንትን ያቃጥል ነበር፡፡ መዝሙረ ዳዊት በውስጡ የያዘው ሚሥጢር እጅግ ጥልቅ ነው፡፡ አባቶቻችን ዛሬም በዱር በጫካ ሆነው መዝሙረ ዳዊትን አብዝተው ይደግማሉ፡፡ እንኳንስ የሰው ልጅ ይቅርና ‹‹መዝሙረ ዳዊትን›› ሰማያውያን ቅዱሳን መላእክትም እግዚአብሔርን ለማመስገኛነት ተጠቅመውበታል፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እድሜ ዘመኑን እግዚአብሔርን በማገልገልና በመፍራት ኖሮ በታኅሣሥ 23 ቀን በሰላም ዐርፎ በኢየሩሳሌም ተቀብሯል፡፡ የቅዱስ ዳዊት ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!